#FastMereja I የወተት ምርት እና ማቀነባበሪያ ድርጅት የሆነው ሆላንድ ዴይሪ የ2019 ዓ.ም የታላቁን የወተት አቅራቢዎች ቀን በቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ፋብሪካው አክብሯል። በዕለቱ የኢትዮጵያን የወተት ዘርፍ ለማሳደግ፣ የምግብ ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም በባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን መተማመን ለማጠናከር የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። መድረኩ ከዋነኛ የወተት መሰብሰቢያ ቀጠናዎች የተወጣጡ 46 ቁልፍ የወተት ሕብረት ሥራ ማኅበራት መሪዎችን፣ የግል አቅራቢዎችን እና የወተት መሰብሰቢያ ጣቢያ አስተባባሪዎችን በአንድ ላይ ያገናኘ ነበር።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ፣ ሆላንድ ዴይሪ በየቀኑ ከ6 ክልሎች ከሚገኙ ግምታዊ 7,000 አርሶ አደሮች በሕብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ጥራቱን የጠበቀ ወተት ይሰበስባል። የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥም ወተቱ ትኩስ፣ ንጹሕ እና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆን እንዳለበት አጽንዖት ተሰጥቶበታል። በዚህም መሠረት ድርጅቱ ወተትን በጣቢያዎች መቀበያ ፈተና፣ ፈጣን የኤም.ሲ.ፒ ፍተሻ እና በፋብሪካ ውስጥ ጥልቅ የላቦራቶሪ ምርመራዎችን (አፍላቶክሲን፣ ኤስ.ሲ.ሲ፣ አይ.ቢ.ሲ እና አንቲባዮቲኮችን ጨምሮ) የሚያከናውንባቸው ጥብቅ የጥራት መመዘኛዎች መዘርጋቱ ተገልጿል። በተደረጉ የጋራ ጥረቶችም ከዓመታት በፊት ይስተዋሉ የነበሩ እንደ አንቲባዮቲክ መበላሸት እና በውሃ የማቀለጥ ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸው ተነግሯል።
ድርጅቱ እስከ እ.ኤ.አ. 2030 ድረስ ያስቀመጠውን የሽያጭ ግብ ለማሳካት በየቀኑ የሚሰበስበውን የጥሬ ወተት መጠን ወደ 105 ኪሎ ሊትር ለማድረስ አቅዷል። የተለያዩ የዮጎት ዓይነቶችን፣ የጎዳ አይብ፣ ፓስተር የተደረገ ወተት እና ቅቤን እያመረተ የሚገኘው ሆላንድ ዴይሪ፤ ምርቶቹን በለቡ እና በድሬዳዋ መጋዘኖች በኩል ለአዲስ አበባ፣ ለደብረ ዘይት፣ ለአዳማ፣ ለመቐለ እና ለጅጅጋ ገበያዎች እያከፋፈለ ይገኛል። የመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እና የሥራ ሃላፊዎች የወደፊት የልማት ዕቅዶችን ያቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች የፋብሪካ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ አቅራቢዎች የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።




