#FastMereja I በዓለም አቀፍ ደረጃ በሪል እስቴት ልማት ዘርፍ ስመጥር የሆነው ሪፖርታዥ ግሩፕ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ የሚገነባው “ሪፖርታዥ ታወርስ” የተሰኘው የቤት ልማት ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥና የቁፋሮ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሳር ቤት አፍሪካ ሕብረት ፊት ለፊት በሚገኘው ቦታ ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት፡ ከ1,000 በላይ ዘመናዊ የመኖሪያ ክፍሎችን፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የስፖርት ማዕከላትንና ሌሎችንም ዘመናዊ የአገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ምቹ የክፍያ አማራጮችንም ይዞ ቀርቧል ተብሏል። በአጠቃላይ 55ሺ ቤቶች የሚገነቡ ይሆናል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተገለጸው፡ በመዲናችን አዲስ አበባ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ጋር ተያይዞ ያለውን ከፍተኛ የቤት ፍላጎትና ክፍተት የመንግሥት አቅም ብቻውን መሸፈን ስለማይችል፣ የሕዝብና የግል አጋርነትን በማጠናከር ረገድ ፕሮጀክቱ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ የጋራ አልማት በኢትዮጵያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች (UAE) መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በቤት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአቅም ግንባታ ዘርፎች የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል።
በ2014 እ.ኤ.አ በአቡ ዳቢ የተመሠረተውና በ25 ሀገራት ውስጥ ከ116 በላይ ፕሮጀክቶችን የገነባው ሪፖርታዥ ግሩፕ ያለውን ሰፊ ዓለም አቀፍ ልምድ በመጠቀም ግንባታውን በከፍተኛ ጥራትና በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ አጠናቆ ለሕዝብ ጥቅም ያውላል ተብሎ ይጠበቃል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ፋውንዴሽኑም የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የግንባታውን ሂደት በቅርበት እንደሚከታተሉና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።




