banner

የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ሀብት ከ624 ቢሊዮን ብር ማለፉ ተገለጸ፤ ባንኩ ታሪካዊ የተባለ የ38.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አ

የአዋሽ ባንክ ጠቅላላ ሀብት ከ624 ቢሊዮን ብር ማለፉ ተገለጸ፤ ባንኩ ታሪካዊ የተባለ የ38.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አግኝቷል

#FastMereja I አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2026 በነበረው የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ሀብቱን ከ624 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረሱን አስታወቀ። ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ በግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን 38.3 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ማስመዝገቡንም ገልጿል።

ጥቅምት 21 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል በተካሄደው የባንኩ 31ኛ መደበኛ እና 19ኛ አስቸኳይ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉሬ ኩምሳ የዓመቱን አፈጻጸም ይፋ አድርገዋል። እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ181.4 ቢሊዮን ብር ወይም የ41 በመቶ ዕድገት በማሳየት በሀገሪቱ የግል ባንኮች ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

በተመሳሳይ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል 38.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም የብሔራዊ ባንክን መስፈርት በቀዳሚነት ማሟላቱንና በዘርፉ ቀዳሚ አድርጎታል። ባንኩ በበጀት ዓመቱ 84.6 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑም በ41 በመቶ እድገት በማሳየት 469.3 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል። የብድር መጠን በ54.5 ቢሊዮን ብር በመጨመር 274.1 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ 2.6 ቢሊዮን የካናዳ/አሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሪ መገኘቱም ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል አዋሽ ባንክ በ2018 የበጀት ዓመት 15.77 ቢሊዮን ብር የገቢ ግብር በመክፈል ከሀገሪቱ ከፍተኛ ግብር ከፋይ የግል ተቋማት አንዱ መሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም ባንኩ በግሎባል ፋይናንስ መጽሔት ለ5ኛ ጊዜ “የኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ” ተብሎ የተመረጠ ሲሆን፣ በታይላንድ ባንኮክ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የWSBI-ESBG የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ሽልማትን ለ2ኛ ጊዜ ተቀብሏል። ባንኩ ለማህበራዊ ኃላፊነት መወጫ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም በሪፖርቱ አመላክቷል።





Leave a Comment