banner

በአማራጭ እንክብካቤ ያደጉ ወጣቶችን ከእንክብካቤ በኋላ ለመደገፍ ብሔራዊ ፖሊሲ ያስፈልጋል ተባለ!

#Fastmereja:-በኢትዮጵያ በአማራጭ የሕፃናት እንክብካቤ ተቋማት አድገው ወደ ገለልተኛ ሕይወት የተሸጋገሩ ወጣቶችን (Care Leavers) መብትና ጥቅም ለማስከበር የተቋቋመው “የብሔራዊ አማራጭ እንክብካቤ ተቋማት ያደጉ ማህበራት ጥምረት” 2ኛውን የ“ኬር ሊቨርስ” ቀን «ከተሞክሮ ወደ አቅም ግንባታ፤ ከአቅም ግንባታ ወደ አመራር» በሚል መሪ ቃል በዛሬዉ እለት በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።

በበዓሉ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የብሄራዊ አማራጭ እንክብካቤ ተቋማት ያደጉ ማህበራት ጥምረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ምስክር ታደሰ እንደገለፁት፣ ወጣቶች ከእንክብካቤ ማዕከላት በሚወጡበት ወቅት በቂ ዝግጅትና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ካልተደረገላቸው ከፍተኛ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው አስገንዝበዋል።

አቶ ምስክር አክለውም የትምህርትና የሙያ ስልጠና ተደራሽ አለመሆን፣ የሥራ ዕድል እጥረት፣ የመኖሪያ ቤት ማጣት፣የገቢ ምንጭ ክፍተት፣ የስነ-ልቦና ድጋፍ ማነስ እንዲሁም ከማህበረሰቡ ዘንድ የሚደርስባቸው መገለልና ተገቢ ያልሆኑ ቅጥያዎች መለጠፍ ወጣቶቹን የሚያጋጥሙ ዋና ዋና ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኬር ሊቨርስን ትክክለኛ ቁጥር፣ የኑሮ ሁኔታና ፍላጎት የሚያሳይ የተሟላ ብሔራዊ ጥናት አለመኖሩ ለፖሊሲ ቀረጻ እንቅፋት መሆኑን በጥምረቱ መግለጫ ላይ ተመልክቷል።

ጥምረቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የወጣቶችን ድምፅ ለማሰማት፣ ሕጋዊ ምዝገባ በማግኘት፣ የበዓላትና የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅቶችን በማካሄድ፣ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከልማት አጋሮች ጋር በመስራት፣ እንዲሁም የተለያዩ የክህሎትና የስነ-ልቦና ድጋፎችን በመስጠት በርካታ አዎንታዊ ተግባራትን ሲያከናው መቆየቱ ተገልጿል።

ሆኖም የኬር ሊቨርስ የሕይወት ሽግግር በአንድ ተቋም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ፣ ጥምረቱ በጥናት የተደገፈ ብሔራዊ የመረጃ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ እና አገራዊ የሽግግርና የድህረ-እንክብካቤ ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ተግባር እንዲገባ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት፣ በሲቪል ማህበራት፣ በግሉ ዘርፍና በልማት አጋሮች መካከል የተቀናጀ አጋርነት እንዲኖር፣ የትምህርት፣ የሥራ ስምሪት፣ የመኖሪያ ቤትና የጤና አገልግሎቶች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኛ ወጣቶች የተለየ ድጋፍ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም ሚዲያዎች የወጣቶችን ድምፅ ለህዝብና ለፖሊሲ አውጪዎች በማድረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

በመጨረሻም የእንክብካቤ ተሞክሮ የወጣቶችን የወደፊት ዕጣ እንደማይወስን እና ኬር ሊቨርስ የድጋፍ ተቀባይ ብቻ ሳይሆኑ የማህበረሰብ አበርክቶ አድራጊዎችና የነገ መሪዎች መሆናቸውን በማስገንዘብ መልእክቱን አስተላልፏል።





Leave a Comment