#Fastmereja:-በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ መሠረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጠቅላላ ሀብት ከ10 ቢሊዮን ብር ማለፉን የአዲስ አበባ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ይኸንን የገለጸው ዓለም አቀፍ የቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ቀንን አስመልክቶ በዛሬዉ እለት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ነው።
በዘንድሮው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ78ኛ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረው ይህ በዓል “የኅብረት ሥራ ፋይናንስ ለተረጋጋ ኢኮኖሚ አለም ልዩ ምልክት ናቸዉ” (Cooperative Finance: A Steady Signal in a Noisy World) በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
በዘንድሮው ዓመት በዓል አከባበር ሂደት ከወረዳ ጀምሮ በተከናወኑ ውይይቶች እና በሶስተኛው ሳምንት ዙሪያ በሚደረጉ የበዓል ስነ-ስርዓቶች ላይ ከጥቂት መቶዎች ጀምሮ እስከ 10,000 የሚደርሱ አባላትና የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ስራ ዩኒየኖች ያሉ ሲሆን ከ291,448 በላይ አባላትን ማቀፍ የቻሉ እና ከአስር ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሀብት ማፍራት የቻሉ ከ1106 በላይ የሚሆኑ መሰረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የሚገኙ ሲሆን አጠቃላይ የማኅበራቱ የብድር አቅርቦት አቅም በየዓመቱ በአማካይ 2.7 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል።
በኢትዮጵያ ደረጃ ከ18,500 በላይ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከ8 ሚሊዮን በላይ አባላትን በማቀፍ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የቁጠባና አክሲዮን ገንዘብ ማሰባሰብ የቻሉ ሲሆን፣ ከ45 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በመስጠት ለአገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት አዎንታዊ ድርሻ እያበረከቱ እንደሚገኙ በመግለጫዉ ተብራርቷል።
ዓለም አቀፉ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ምክር ቤት (WOCCሀ)(2025) መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በዓለም ዙሪያ በ93 አገራት ውስጥ የሚገኙ 61 ሺህ 838 ማኅበራት ከ419 ሚሊዮን በላይ አባላትን በማቀፍ 3.979 ትሪሊዮን ዶላር ጠቅላላ ሀብት እንደሚያንቀሳቅሱ ተገልጿል።
የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ አሠራራቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ፣ ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት፣ ዲጂታል የሂሳብ አያያዝን በመተግበር እና ብድርን መሠረት ያደረገ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ለአባላቶቻቸው በማመቻቸት ዘላቂ የፋይናንስ ተቋም የመገንባት አቅጣጫ ይዘው እየሠሩ እንደሚገኙ ነዉ የተገለፀዉ።




