#FastMereja
ማክሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2016 ዓ.ም 25 ኢትዮጵያውያን እና 2 የመናዊያንን አሳፍራ ከጅቡቲ የተነሳችው የስደተኞች ጀልባ ዱባብ አቅራቢያ ልዩ ስሙ ባኒ አል ሃካም አከባቢ ተገልብጣ መስጠሟን በየመን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ዘግቧል። አደጋውን ተከትሎም 13 ሰዎች በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ የተቀሩት 14ቱ ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል።
ከሟቾች መካከል አስራአንዱ ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። የሟቾቹ አስከሬን በዱባብ አከባቢ አልሹራ አቅራቢያ የሚገኘው ባብ-ኤል መንደብ የባህር ዳርቻ ላይ ተገኝቷል። በስፍራው ያሉ የነፍስ አድን ሰራተኞች የቀሪዎቹን ስደተኞች አካል የማፈላለግ ስራ እስከአሁን እንደቀጠሉ ነው።
ምንም እንኳን የዚህች ጀልባ የመሰበር እና መገልበጥ መነሻ ግልጽ ባይሆንም፣ በዚህ መስመር በሚያጋጥመው ከባድ ማዕበል ምት እና የጀልባ አቅም ውስንነት ምክንያት በተደጋጋሚ የጀልባ መሰበር፣ መገልበጥ እና መስጠም አደጋ እየደረሰ ይገኛል። ይህን ለመከላከል በየጊዜው ለህብረተሰቡ የሚሰጡ ብዙ ማስጠንቀቂያዎች ቢኖሩም፣ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት በየቀኑ የሰዎችን ህይወት እያጣን ይገኛል።
እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በዚህ ምስራቃዊ መስመር ላይ ብቻ 693 ሰዎች በባህር ላይ የሰጠሙትን ጨምሮ 2,082 የስደተኞች ሞት ተዝግቧል።
በአሁን ወቀት በየመን ያለው አለመረጋጋት እየጨመረ ቢሄድም ከዚህ በተቃራኒ ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ወደዚህ ስፍራ የሚያደርጉት ጉዞ እየተበራከተ መምጣቱን IOM ዘግቧል።
በቅርቡ እንኳን በሰኔ እና በሐምሌ ወር በዚህ ስፍራ በተመሳሳይ በደረሰው የጀልባ መሰበር እና መገልበጥ አደጋን ተከትሎ በርካታ ዜጎቻችን በባህር ላይ ቀርተዋል ሲል የኢትዮጵያ ኤምባሲ በጂቡቲ ገልጿል።
