banner

በኮሬ ዞን በእገታ ላይ የነበሩ አራት አርሶ አደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አራት አርሶ አደሮች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሟች ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ ፡፡ ታጣቂዎቹ ግድያውን ትናንት ሐሙስ የፈጸሙት አርሶ አደሮቹን ለመልቀቅ በመያዣነት የጠየቁትን አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተቀበሉ በኋላ ነው ተብሏል ፡፡

አርሶ አደሮቹ የታገቱት ትናንት ሐሙስ ማለዳ ከብት እያሠማሩ ባሉበት ወቅት መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሦስት የሟች የቅርብ ዘመዶች «ታጣቂዎቹ ወደ ቀበሌው የገቡት ከአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመነሳት ነው ፡፡ ታጋቾቹን ከያዙ በኋላ ካሊያ ተብሎ ወደ ሚጠራው ጫካ ውስጥ ነው ይዘው የሄዱት ፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር እና አንድ ካርቶን የትምባሆ ሲጋራ ከተሰጣቸው እንደሚለቋቸው መልዕክት ልከውብን ነበር ፡፡ በተጠየቅነው መሠረት የተባልነውን ብንልክም ገንዘቡን እና ትምባሆውን ከተቀበሉ በኋላ ገድለዋቸው ሄደዋል ፡፡ ቀብራቸውም ዛሬ ዓርብ እየተፈፀመ ይገኛል» ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በአርሶ አደሮቹ ግድያ ላይ የኮሬ ዞን አስተዳዳሪንም ሆነ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አመራሮቹ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ያም ሆኖ የአርሶ አደሮቹን መገደል በተረጋገጠ የፌስ ቡክ ገጹ የገለጸው የዞኑ መስተዳድር የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ቡድኖች ናቸው ሲል ዐሳውቋል ፡፡

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በኮሬ ምርጫ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ ዶክተር ዐወቀ ሀምዛዬ እገታና ግድያውን የፈፀሙት አካላት በቁጥር 16 አካባቢ የሚሆኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን ከነዋሪዎች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል ፡፡ በአካባቢው ግድያና ጥቃት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም የጠቀሱት ዶክተር ዐወቀ «መፍትኄው ሁለት ነው ፡፡ እሱም የፀጥታ ኃይሉ ጠንካራ ዘመቻ በማድረግ ታጣቂዎችን ማጽዳት ወይም ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል በሕጋዊ መንገድ ማስታጠቅ ያስፈልጋል» ብለዋል ፡፡

ዘገባው የዶቼ ቬለ ነው።

10 comments

Sultan Radi Radi Sultan September 13, 2024 - 11:12 am

አይ ይች ሀገር

Reply
Yared Tesfaye Yabaye Lij September 13, 2024 - 11:12 am

መቼ ነው ግን ከሞት ከስቃይ የምናርፈው

Reply
Amanuel Worku September 13, 2024 - 11:16 am

የኮሬ ህዝብ በታጣቂዎች ግደያ ተሰቃይቷል !!!😭😭

Reply
Hábèśhã Xø September 13, 2024 - 11:18 am

እች ናት ሀገሬ🫡😂

Reply
Mahlet Bukulo September 13, 2024 - 11:18 am

💔

Reply
Aschilo Endeshaw September 13, 2024 - 11:18 am

ነብስ ይማር

Reply
Tesfaye Taye September 13, 2024 - 11:18 am

ነፍስ ይማር።

Reply
Johnny Abakiya September 13, 2024 - 11:20 am

በጣም ያሳዝናል !

ህዝብ እራሱን እንዲከላከል በህጋዊ መንገድ ማስታጠቅ ያስፈልጋል ፤
አከተመ ።

Reply
Ephrem Mesfin September 13, 2024 - 11:20 am

ራሱን ይከላከላል የተሻለ ነዉ

Reply
Amanuel Umer September 13, 2024 - 11:24 am

ምነው በአለህ መከራ፣ሞት እና ሰቀቀን በ2016 ትተን ወደ 2017 ተሻግረናል እያልን መርዶ ሰማንና ማረን 😢

Reply

Leave a Comment