#FastMereja I ከሶስት አስርት አመታት በፊት የባህር በር ያጣችው ኢትዮጵያ፤ በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ እያከናወነች ያለውን የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ግንባታ በቅርቡ እንደምታጠናቅቅ ተዘግቧል። የጠቅላይ መምሪያው ግንባታ 95 በመቶ መተናቀቁን ስፑትኪክ አፍሪካን ጠቅሶ አፍሪካ ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ይህም ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም ብሔራዊ የባህር ኃይልን ዳግም ለመገንባት ያላትን ምኞት የሚያሳይ አንዱ እርምጃ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።
በሦስት ሄክታር ስፋት ላይ የተገነባው ባለ አራት ፎቅ የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ሕንፃ፤ አስተዳደራዊ ቢሮዎችን፣ የሕክምና ክሊኒክን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን፣ የስፖርት ተቋማትንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን የሚያካትት ሲሆን ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ መሠረት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።
በተጨማሪም ይህ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ተፅዕኖ መልሳ ለማግኘት ለማግኘት የምታደርገው ስትራቴጂ አካል ነው ተብሏል።
ከጎርጎሮሳውያኑ 1993 ጀምሮ ወደ የባህር በር ብታጣም፣ የኢትዮጵያ መንግስት የባህር ኃይል አቅሞች የንግድ መንገዶችን ለመጠበቅ፣ ለአለም አቀፍ የባህር አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት እና በጂቡቲ እና በሱዳን ወደቦች በኩል ወደ ዓለም አቀፍ ውሃዎች መድረስን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጿል።
በመጋቢት ወር ኢትዮጵያ ከሩሲያ መንግስት ጋር የባህር ኃይል ልማትን እና ስልጠናን ለመደገፍ የትብብር ስምምነት ተፈራርማለች። ይህ ስምምነት የተደረገው ቀደም ሲል ከፈረንሳይ ጋር የነበረው የባህር ኃይል አጋርነት መቋረጡን ተከትሎ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።
በጊዜው የሩሲያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ አድሚራል ቪላዲሚር ቮሮቢቭ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የሚገነባቸውን የባሕር ኃይል ተቋማት ጠቅላይ መምሪያውና ቢሾፍቱ የሚገኘውን ማሰልጠኛ ማዕከል ጎብኝተው፤ የኢትዮጵያን የባህር ኃይል አቅም ለማጠናከር ሞስኮ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
ዘገባው የአዲስ ስታንዳርድ ነው

