የ12ኛ ክፍል ፈተናን ከወሰዱ ከ581 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ፈተናውን ማለፍ የቻሉት 48,929ኙ ናቸው፤ 1,249 ት/ቤቶች ምንም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀርተዋል
#FastMereja I በ2017 የትምህርት ዘመን የተሰጠውን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 581 ሺህ 905 ተማሪዎች መካከል ፈተናውን ማለፍ የቻሉት 48,929ኙ ወይም 8.4 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ውጤትን አስመልክተው በዛሬው ዕለት መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በዚህም ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 8.4 በመቶ ወይም 48,929 ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የገለጹት ሚንስትሩ ከእነዚህም ውስጥ 30,451 የሚሆኑት ወንድ ተማሪዎች ሲሆኑ 18,478ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት አማካይ ውጤት 29 ነጥብ 7 እንደነበር አስታውሰው÷ ዘንድሮ 31 ነጥብ 67 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ከፍተኛ ተማሪዎችን ያሳለፉ ክልሎችም አዲስ አበባ፣ ሐረሪ እና አማራ ክልል ናቸው ብለዋል።
የ2017 ዓ.ም ከፍተኛ ውጤት በተፈጥሮ ሳይንስ የተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው ከ600/ 591 በማምጣት ዶዶላ ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት የሚማር ወንድ ተማሪ ውጤቱን ማስመዝገቡን አመላክተዋል።
ከሴት ከፍተኛው ውጤት በተመሳሳይ በተፈጥሮ ሳይንስ የተመዘገበ ሲሆን 579/600 በማምጣት ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነች ሴት ውጤቱን ማስመዝገቧ ተጠቁሟል።
በማህበራዊ ሳይንስ ወንድ 562/600 ከአምቦ ቦርዲንግ ስኩል በማምጣት እንዲሁም ሴት 548/600 ከሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት መሆናቸው ተመላክቷል።
ባለፈው ዓመት ከ500 በላይ ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር 1221 እንደነበረ ያስታወቁት ሚንስትሩ ዘንድሮ 742 ሴት እና 1642 ወንድ በአጠቃላይ 2384 ተማሪዎች 500 እና ከዛ በላይ አስመዝግበዋል ብለዋል። በክልል ደረጃ ሲታይም 888 ተማሪዎች ከአዲስ አበባ: 794 ኦሮሚያ እና 385 ተማሪዎች ደግሞ ከአማራ ክልል ከ500 በላይ ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ዘንድሮ 1,249 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ ሳያሳልፉ ቀርተዋል ያሉ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነጻጸር 114 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በማሳለፍ መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል።
via አዲስ ስታንዳርድ

4 comments
ብርሃኑ ነጋ ይሄ ለሊት አይንጋልክ የወጣቱን ተስፋ እንዳጨለምክ ይጨልምብክ
የትምህርት ሚኒስቴር ስራ አስተምሮ ማብቃት ወይስ የወደቀ ተማሪ መቁጠር?
ብራሃኑ ነጋ ከወትሮው 3 እጥፍ ለውጥ አለ ደስ ይላል።
መቼ ነው ግን ይሄ ሰውዬ ለትምህርት ውድቀቱ እኔም ተጠያቂ ነኝ የሚለው እና ስልጣን የሚለቀዉ?