#FastMereja I ዛሬ ህዳር 30/2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከታህሳስ 3 እስከ 6/ 2018 ዓ.ም ድረስ ቤት ለቤት በሚካሄደው አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ላይ ትኩረት ያደረገ ውጤታማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሂዷል።
የመድረኩ ዋና ዓላማ ክትባቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እንዲሆን ለማስቻል፤ በዘመቻው አፈጻጸም ላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና ማጠናከር ነዉ።
በመድረኩ ላይ ለህዝብ ተደራሽ የሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዉ የዘርፉ ባለሙያዎችም የተለያዩ ገለፃዎች ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ እንደገለጹት፣ ዘመቻው የፖሊዮ ስርጭትን ሙሉ በሙሉ በመከላከል ጤናማ ትውልድን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ሁሉም ነዋሪዎች፣ በተለይም የሕፃናት ወላጆችና አሳዳጊዎች፣ ቤት ለቤት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን ተቀብለው እድሜያቸው ከ5 ዓመትና ከ 5 አመት በታች የሆኑ ህጻናትን በሙሉ እንዲያስከትቡ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ከ25 ሚሊየን በላይ ህፃናት ክትባቱን ይከተባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እና ክትባቱ በአፍ ጠብታ እንደሚሰጥ ተገልፆ በክትባት ዘመቻዉ ላይ ስለ ማርቨርግ በሽታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ለህብረተሰቡ እንደሚሰጥ ተገልጿል።
የፖሊዮ በሽታ እጅግ አደገኛና ትውልድን ለአካል ጉዳት በመዳረግ በማህበረሰቡ ላይ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያስከትል በመሆኑ ህፃናትን በማስከተብ ልንከላከለው እንደሚገባ ተገልጿል።




