#FastMereja I የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከር የጀመረው ብዙዎች እንደሚሉት በባህር በር ጥያቄ ምክንያት ሳይሆን፣ በትግራይ ጦርነት ወቅት የኤርትራ ጦር በፈጸማቸው ተግባራት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የነበረው አለመግባባት የጀመረባቸውን ነጥቦች በዝርዝር አስረድተዋል።
የቅራኔው መነሻ ነጥቦች
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ጸቡ የጀመረው የቀይ ባህር ጉዳይ ከመነሳቱ ቀደም ብሎ በጦርነቱ የመጀመሪያ ዙር ወቅት ነው። ለቅራኔው መባባስ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውንም ነጥቦች እንዲህ ዘርዝረዋል፦
የንብረት ውድመት፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሽሬን ከተቆጣጠረ በኋላ የኤርትራ ጦር ተከትሎ በመግባት የግለሰቦችን ቤቶች እና ፎቆች ማፍረስ መጀመሩ።
የጅምላ ጭፍጨፋ፦ የአክሱም ከተማ በተያዘችበት ወቅት በወጣቶች ላይ የተፈጸመው የጅምላ ረሸን “ጸቡን አፋፍሞታል” ብለዋል።
የፋብሪካዎች ዘረፋ፦ በአድዋ እና በአዲግራት የሚገኙ ፋብሪካዎችን (የመድኃኒት ፋብሪካን ጨምሮ) የመነቃቀል፣ የመሰረቅ እና የማፈራረስ ተግባራት መፈጸማቸው ጸቡን ጫፍ ላይ እንዳደረሰው ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊቱ እንዲቆም በተደጋጋሚ መልዕክተኞችን ወደ አስመራ መላካቸውን አስታውቀዋል።
”የላኳቸው የትግራይን ሕዝብ ‘ሕዝቤን አታጎሳቅሉ’ ብዬ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሁለት ጊዜ ወደ ኤርትራ ተልከው እንደነበርና የምክክር ሒደቱንም እርሳቸው፣ መንግስት እና ሻዕቢያ እንደሚያውቁት ተናግረዋል።
”አንዳንድ ሰዎች ችግሩ የተፈጠረው ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በማንሳቷ ነው ይላሉ፤ ነገር ግን አይደለም” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፣ የባህር በር ጥያቄው ከመነሳቱ በፊት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በንብረት ውድመት ምክንያት ግንኙነቱ ተበላሽቶ እንደነበር አስገንዝበዋል።
