#FastMereja I በኬንያ በተለይ በታዋቂ ሰዎችና በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዘንድ እየተለመደ የመጣው የብር ኖቶችን እንደ አበባ በማሸብረቅ ለስጦታ ማቅረብ፣ አሁን ላይ ከህግ ጋር የሚያጋጭ ተግባር ሆኗል።
የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ (CBK) ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ የሀገሪቱን ገንዘብ በማጠፍ፣ በመለጠፍ፣ በስቴፕለር በመምታት ወይም በሌሎች ማጣበቂያዎች በማያያዝ የገንዘቡን ይዘት ማበላሸት በህግ እንደሚያስቀጣ አስታውቋል።
የሀገሪቱን ህጋዊ መገበያያ ገንዘብ ያበላሸ ማንኛውም ሰው ተይዞ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 7 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ባንኩ አስገንዝቧል።
ገንዘቡ በሚታጠፍበትና በሚያያዝበት ወቅት ስለሚጎዳ፣ ባንኮች በሚጠቀሙባቸው የገንዘብ መቁጠሪያ ማሽኖችና በኤቲኤም (ATM) ውስጥ ለማለፍ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ይህም ገንዘቡን በአዲስ ለመተካት ለባንኩና ለህዝቡ አላስፈላጊ ወጪ እያስከተለ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው የፍቅረኛሞች ቀን (Valentine’s Day) እየቀረበ ባለበት ወቅት በመሆኑ፣ በኬንያውያን ዘንድ የተለያዩ አስተያየቶችን አስከትሏል፦
አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች “ማዕከላዊ ባንክ ለዘንድሮው የፍቅረኛሞች ቀን ወንዶችን ከትልቅ ወጪ አድኗል” በማለት በሳቅ የታጀበ አስተያየት ሰጥተዋል።
ኬንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአበባ ምርቷ የምትታወቅ በመሆኑ፣ “ገንዘብን ከማበላሸት ይልቅ እውነተኛውን የተፈጥሮ አበባ መጠቀም ይሻላል” የሚሉ ወገኖችም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ማዕከላዊ ባንኩ ገንዘብን በስጦታ መልክ መስጠትን እንደማይቃወም፣ ነገር ግን የገንዘቡን ይዘትና ጥራት በማይነካ መልኩ መሆን እንዳለበት መክሯል።
