#Fastmereja I የቱሪዝም ሚኒስቴር ከቲክቶክ (TikTok) Creative አዋርድ አዘጋጆች ጋር በመተባበር የሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስተዋወቅና መልካም ገጽታን ለመገንባት የሚያስችል “G-power Face of Ethiopia”የተሰኘ ፕሮጀክት በዛሬዉ እለት ይፋ አድርጓል።
ይህ ፕሮጀክት በዋናነት የሀገሪቱን የቱሪስት መስህቦች በዘመናዊ የዲጂታል አማራጮች ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን፣ ይህም በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ መነቃቃትን በዘርፉ ላይ እንደሚፈጥር በቱሪዝም ሚኒስቴር የፕሮሞሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ተሾመ ተክሉ ገልጸዋል።
የ”Face of Ethiopia” ስራ አስኪያጅ መቅድም ደረጀ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የቁንጅና ውድድርን ያካተተ ቢሆንም ሂደቱ ከተለመደው የውበት ውድድር በተለየ መልኩ የሚካሄድ ነው፡፡
የአምባሳደርነት ስልጠናዉ ተወዳዳሪዎች የወከሏቸውንና የሌሎች ክልሎችን ባህል፣ ታሪክና እምቅ የቱሪዝም አቅም በሚገባ እንዲያውቁ የሚያስችል ጥልቅ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡
ይህም ወጣቶች የሀገራቸው እውነተኛ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆን ዘርፉን እንዲያግዙ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ በጠቅላላ 55 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን ውድድሩም ለ6 ወራት የሚቆይ ሲሆን፣ አሸናፊውም የ 5 ሚሊዮን ብር ከፍተኛ ሽልማት ይበረከትለታል።
የውድድሩ ዋና መመዘኛ ተወዳዳሪዎች “የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች በምን መልኩ አሳውቀዋል?” የሚለው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ይህም በውበት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና በፈጠራ የታጀበ ውድድር መሆኑን ያሳያል።
ይህ አዲስ ጅምር ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የተፈጥሮና የታሪክ ጸጋዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነዉ የተገለፀዉ።




