#FastMereja I በአውሮፕላን ንግድ እና በሀብት አስተዳደር ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም ያተረፈው “ኤርክራፍት ፋይናንስ ጀርመን” (AFG) እህት ኩባንያ የሆነው ኤ ኤፍ ጂ አቪዬሽን አየርላንድ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አፍሪካ ገበያ በይፋ መግባቱን አስታወቀ።
ኩባንያው ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ለአፍሪካው ስራው ልዩ ትኩረት በመስጠት ሁለት ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎችን በአህጉሪቱ ተገኝተው እንዲሰሩ መድቧል። ኩባንያው ወደ አፍሪካ ለመግባት የወሰነው በናይጄሪያው “ካሊ ኤር” ሁለት ሲአርጄ-1000 (CRJ1000) አውሮፕላኖች ባለቤት እንዲሆን ካደረገ በኋላ በአህጉሪቱ ባለው ከፍተኛ ፍላጎት መነሳሳቱን ገልጿል።
የኩባንያው የቢዝነስ አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ክርስቲያን ሃትጄ እና ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና ዋና ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር የሆኑት ሺኤኩማ ጌማዴ የአፍሪካን ስራ እንዲመሩ ተመድበዋል። ባለሙያዎቹ በአውሮፕላን ንግድ፣ በሊዝ፣ በፋይናንስ እና በአየር መንገድ ስትራቴጂ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው።
ባለሙያዎቹ በሚቀጥሉት ወራት በአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት በማድረግ ከአየር መንገዶች፣ ከመንግሥት የዘርፉ ኃላፊዎች እና ከኦፕሬተሮች ጋር በቀጥታ ውይይት እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።
ኩባንያው የንግድ አውሮፕላኖች ግዢ፣ የፕራይቬት ጄት ግብይት፣ የፋይናንስ ሊዝ መፍትሔዎች፣ የበረራ ማዘመን ስትራቴጂ እና የማማከር አገልግሎቶችን ለአፍሪካ ገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
የኩባንያው የአፍሪካ ስራ መሪ ክርስቲያን ሃትጄ “አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ የአቪዬሽን እድገት እየታየባት ያለች አህጉር ናት” ያሉ ሲሆን፣ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው ሺኤኩማ ጌማዴ በበኩላቸው “በአህጉሪቱ የታየው የትብብር ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ዘላቂ የአቪዬሽን ልማትን ለመደገፍ የካበተ ልምዳችንን ይዘን ቀርበናል” ብለዋል።
ይህ የኩባንያው እርምጃ የአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ፍጥነት እየተቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነ ተገልጿል።


