#Fastmereja: ኪ ሃውሲንግ ፋይናንስ ሶሉሸን ዛሬ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በጌትፋም ሆቴል ባከናወነው መርሐግብር ለ300 አዳዲስ አባላቱ የቤት ዕጣ አውጥቷል።
በዕጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ 45 ሰዎች ባለ 1 መኝታ፣105 ሰዎች ባለ 2 መኝታ፣ እንዲሁም 150 ሰዎች ባለ 3 መኝታ ቤቶች ዕጣ ወጥቶላቸዋል፡፡
ተቋሙ ተግባራዊ እያደረገ ያለው “Economies of Scale” ላይ የተመሰረተ የፋይናንስ ሞዴል፣ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በዝቅተኛ ቅድመ-ክፍያ እና ከ2 ሺህ ብር በሚጀምር ወርሃዊ ቁጠባ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡
ኪ ሃውሲንግ ወደ ገበያው ከተቀላቀለ ጀምሮ እስካሁን በአዲስ አበባ በሚገኙ ሰባት ሳይቶች እና በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ ሁለት ሳይቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቱን የቤት ባለቤት ማድረግ መቻሉን በዕለቱ በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
በአሁኑ ወቅት የተቋሙ አባላት ቁጥር ከ20,000 በላይ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይም ”ኪ መንደር” የተሰኘ መጠነ ሰፊ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ለመጀመር አስፈለጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል።
ይህ የዕጣ አወጣጥ መርሐግብር የቤት ፈላጊዎችን ተስፋ የሚያለመልም ከመሆኑም ባለፈ፣ የግል ዘርፉ በቤት ልማት ረገድ ያለውን ሚና የሚያሳይ እንደሆነ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡




