banner

ኢትዮጵያና ጣሊያን በኮንስትራክሽን እና መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች አብሮ ሊሰሩ እንደሆነ ተገለፀ!

#Fastmereja I በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ”የመጀመሪያው የጣሊያን-ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን፣ የኢንፍራስትራክቸር እና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም” ዛሬ መጋቢት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል በደመቀ ሁኔታ ተከፍቷል።

ይህ ከፍተኛ መድረክ በጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር (MAECI) አዘጋጅነት፣ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የጣሊያን ኤምባሲ እና የጣሊያን የንግድ ኤጀንሲ (ITA) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፣ የጣሊያንን የላቀ የቴክኖሎጂ ብቃት ከኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የመሠረተ ልማት ፍላጎት ጋር ለማገናኘት የታለመ ስልታዊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።

በፎረሙ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፣ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ክብርት ማሪያ ትሪፖዲን ጨምሮ ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ሰፊ ምክክር አካሂደዋል።

ፎረሙ በዋናነት”የብሔራዊ የመሠረተ ልማት ልማት አጀንዳ፣የግሉ ዘርፍ እና የአካዳሚ እይታዎች” ዙሪያ የፓናል ዉይይቶች ያካሄደ ሲሆን በጆቫኒ ዲዮጓርዲ (CDP) እና በሀገር ውስጥ የፋይናንስ ባለሙያዎች የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት ድጋፎች ዙሪያ ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።

በግንባታው ዘርፍ የተሰማሩ 25 ታዋቂ የጣሊያን ኩባንያዎች ከመድረኩ ጎን ለጎን ከሀገር በቀል አልሚዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ባለሀብቶች ጋር ቀጥተኛ የንግድ ትስስር የሚፈጥሩባቸው አራት ልዩ አዳራሾች የተዘጋጁ ሲሆን ውይይቶቹም በከተማ መልሶ ማልማት፣ በኢነርጂ፣ በውሃ እና በአቅርቦት ሰንሰለት (Supply Chain) ዙሪያ የሚያተኩሩ ይሆናል፡፡

ይህ ፎረም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ የንግድ አጋርነት በመቀየር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና ዘመናዊ የከተማ ግንባታን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ትልቅ መሠረት እንደሚጥል ይጠበቃል።





Leave a Comment