#FastMereja I ግብፅ የቀይ ባሕር ወሰን የሌላቸውና የየብስ ሀገራት (ኢትዮጵያን ጨምሮ) በባሕሩ ላይ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ወይም ወታደራዊ የባሕር በር ጥያቄ እንዳያቀርቡ በጽኑ እንደምትቃወም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ አስታወቁ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፣ የየብስ ሀገራት ከወደብ ባለቤት ሀገራት ጋር በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት ለንግድ እንቅስቃሴ የሚሆን የባሕር በር ማግኘት ቢችሉም፣ በቀይ ባሕር ቀጠና ወታደራዊ መገኘት ግን ፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ኢጂፕት ስትሪትስ እንደዘገበው፣ ሚኒስትሩ አብደላቲ በሰጡት ማብራሪያ በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሉ ውሳኔዎችና የደኅንነት አስተዳደር ጉዳዮች የባሕሩ ወሰን ባላቸው ሀገራት ብቻ የሚወሰን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ የካይሮ አቋም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር የሚያደርሳትን ቀጥተኛ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል እንቅስቃሴ አማራጮችን ለመዘርጋት ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጥረት ባደረገችበት ወቅት የተሰጠ ምላሽ እንደሆነም ተመላክቷል።
በተጨማሪም የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸው በቀጠናው ያለውን የማሪታይም ደኅንነትና ሰላም ለማስጠበቅ ከሳውዲ አረቢያ ጋር በቅንጅት እየሰራች እንደሚገኝ ገልጸዋል። የቀይ ባሕርና የአደን ባሕረ ሰላጤ ወሰን ያላቸውን ሀገራት የጋራ ስብስብ በማጠናከር በቀጠናው ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም የደኅንነት ስጋቶች ለመከላከል የጋራ ጥረት እንደሚደረግም ሚኒስትሩ አክለው አብራርተዋል።
