#FastMereja I አዋሽ ባንክ ከዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ማስተርካርድ ጋር በመተባበር የካርድ ተጠቃሚዎች በክፍያዎቻቸው የሚሸለሙበት “ይጠቀሙ፤ ይሸለሙ!” (Spend & Win) የተሰኘ አዲስ የማበረታቻ ዘመቻ ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል። ይህ የሽልማት መርሃ ግብር ከህዳር 9 ቀን 2026 እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2027 ዓ.ም ድረስ ለሰባት ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ ዋና ዓላማውም የዲጂታል ክፍያ አጠቃቀምን ማሳደግ እና ደንበኞች ዕለታዊ ግብይቶቻቸውን በካርድ ሲፈጽሙ ተጨማሪ ጥቅሞች እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል።
በመጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ እንደተገለጸው፣ በዘመቻው አጠቃላይ 61 ሽልማቶች ለተወዳዳሪዎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል 30 ዘመናዊ ስልኮች (iPhone 17 እና Samsung Galaxy S26 Ultra) እንዲሁም 30 ታብሌቶች እና አንድ ኬኒያ የጉዞ ሽልማት ይገኙበታል። የዚህ ግዙፍ የጉዞ ሽልማት አሸናፊ ከአንድ የጉዞ አጋር ጋር ወደ ኬኒያ ሙሉ ወጪው በባንኩ የሚሸፈንበት ጉዞ እንደሚያደርግ አቶ ዮሐንስ መርጊያ ገልጸዋል።
አዋሽ ባንክ የደንበኞቹን ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ለማሟላት እና ዘመናዊ፣ ተደራሽ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። በዚህም መሰረት የባንኩ ዓለም አቀፍ የካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ20,000 በላይ መድረሱን በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ ካርዶችን በመጠቀም ደንበኞች በውጭ ሀገር በኢ-ኮሜርስ ገንዘብ እንዲያወጡ፣ ሆቴል ማረፊያዎችን እንዲያመቻቹ እና በኢ-ኮሜርስ መድረኮች ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም አዋሽ ባንክ ከማስተርካርድ ጋር ባለዉ የትብብር ማዕቀፍ የደንበኞቹን የተለያዩ ፍላጎቶችና የአጠቃቀም ምርጫዎች መሰረት ያደረጉ አዲስ የካርድ ምርቶችን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ከእነዚህም መካከል World Elite Debit፣ Platinum Prepaid፣ Gold Prepaid እና Corporate Prepaid የተሰኙ ዓለም አቀፍ ካርዶች የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ካርዶች ደንበኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉትን የተለያዩ ግብይቶች በቀላሉ፣ በፍጥነት እና በደህንነት እንዲፈጽሙ የሚያስችሉ መሆናቸው በይፋዊ የመነሻ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።




