#FastMereja I በአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦች በተለይም ጥሬ ስጋን ከፍ ባለ ደረጃ ለቱሪዝም መስህብነት ማብቃት እና ሀገራዊ ብራንድ አድርጎ መገንባት ያለመ ታላቅ የምግብ እና የሙዚቃ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ተገለጸ። ዙፋን ኢቨንትስ ከተስፋ ሪቪው ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ይህ ህዝባዊ የጋራ መዝናኛ ፌስቲቫል በመጪው ሕዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም ይካሄዳል።
አዘጋጆቹ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዳመላከቱት እንደ ጣሊያን ፓስታ ወይም የሜክሲኮ ቡሪቶ ሁሉ የኢትዮጵያን ጥሬ ስጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅና ተደራሽ የሆነ እሴት ማድረግ ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። በመሆኑም ይህ ፌስቲቫል ጥሬ ስጋንና የሀገር ውስጥ ባህላዊ ምግቦችን በስፋት በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በዚሁ ዕለት በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ እንደ ዮናስ ጨርጨር፣ ዝቋላ እና ጃሌ ድሬ ያሉ ታዋቂ የስጋ ቤት ተቋማት የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከምግብ ዝግጅቱ ጎን ለጎን የልጆች መጫወቻ ቦታዎች፣ የተለያዩ የጌም እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ታዋቂ አርቲስቶችና የሙዚቃ ባንዶች የሚቀርቡበት ድምቀት ያለው መድረክ ተዘጋጅቷል። ዝግጅቱ ከከተማዋ የኮሪደር ልማት ማዕቀፎች አንዱ በሆነውና ሰፊ የትራፊክ ማቆሚያ ባለው በአፍሪካ ህብረት የገበያ ማዕከል እና ፓርኪንግ አካባቢ ይከናወናል።
ይህ ፌስቲቫል ለዕረፍት እና ለጾም መያዣ ቀን የሚመጥን፣ ህዝብ በጋራ ተሰብስቦ የሚዝናናበት አዲስ የንግድና የመዝናኛ ምዕራፍ እንደሆነ የገለጹት አዘጋጆቹ፤ ወደፊትም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። አዘጋጆቹ አክለውም የጥሬ ስጋ እና የሙዚቃ ወዳጆች በሙሉ በዕለቱ በቦታው በመገኘት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ጥሪ አቅርበዋል።




