banner

“የግንባታ ወጪ መናርና ሕገ-ወጥ አሠራሮች የቤት ልማቱን ፈትነውታል!” የኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር

#Fastmereja:- የመኖሪያ ቤት ዋጋን ከኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም ጋር ተመጣጣኝ ለማድረግ እና የቤት ልማት ዘርፉን ለማነቃቃት፣ የባንክ የቤት ብድር ወለድ ምጣኔ ወደ 7 በመቶ እንዲወርድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን የኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር አስታወቀ።

ማኅበሩ በዛሬዉ እለት በዋና ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀዉ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እስከ 1.5 ሚሊዮን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርስ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እንዳለ ገልፀዉ ይሁን እንጂ ከፍተኛ የባንክ ወለድ እና የረጅም ጊዜ (15 እና 20 ዓመት) የብድር አቅርቦት እጥረት፣ በተለይም ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የቤት ባለቤት እንዳይሆኑ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነ ገልፀዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የሞርጌጅ (የቤት ብድር) ባንኮችን ለማቋቋም የቀረቡለትን የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ተቀብሎ ወሳኝ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አመራሮቹ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ጥናት በኢኮኖሚ ማኅበር ተገምግሞ የሪል ስቴት ደንብ ረቂቅ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴርና የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ካቢኔ) እያመራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በግንባታ ዘርፉ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ ግብዓቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከውጭ ምንዛሬ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ከፍተኛ የዋጋ ንረት መከሰቱ ተገልፆ ባለፉት ሦስት ዓመታት የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ሁለት ሕንፃዎችን ይገነባ የነበረ በጀት ዛሬ አንድ ሕንፃ ብቻ የሚሠራበት ሁኔታ መፈጠሩን ማኅበሩ አስረድቷል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶችን በተለይም የአገር ውስጥ የብረት ማዕድንን በማልማት በአገር ውስጥ ምርት መተካት፣ ለአምራች ፋብሪካዎች የታክስ እረፍት መስጠት፣ የመሬት ልማት መነሻ ዋጋን ማስተካከል እና ቀልጣፋ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ትኩረት የተሰጣቸው አቅጣጫዎች ናቸው፡፡

ማኅበሩ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ አልሚዎችን በአራት ምድቦች ከፍሎ እንደሚመለከት ገልጿል። እነርሱም፦ መሬት ሳይኖራቸው ገንዘብ የሚሰበስቡ «አጭበርባሪዎች»፣ የድሮ ቦታዎችን እንደ አዲስ በመሸጥ (በፖንዚ ስኪም አሠራር) የሚንቀሳቀሱ፣ የራሳቸውን ወጪ ሳያጠኑ የሌሎችን ዋጋ ተከትለው የሚሸጡ እና በዕውቀትና በታማኝነት የሚሠሩ አልሚዎች ናቸው።

የመጀመሪያዎቹን ሁለት ሕገ-ወጥ ምድቦች በአዲሱ የሕግ ማዕቀፍ ለመታገል፣ ሦስተኛውን ወደ ትክክለኛው መስመር ለማምጣት፣ ታማኝ አልሚዎችን ደግሞ በመሬት አቅርቦት ለመደገፍ ከመንግሥት ጋር እየሠራ መሆኑም በመግለጫዉ ተገልጿል።

የገዢዎችን ገንዘብ ከብክነትና ከስርቆት ለመጠበቅም በዝግ ሒሳብ (Escrow Account) መጠቀም እና የግንባታ ጥራት ቁጥጥርን ማጠናከር የግድ መሆኑ ተገልፆ በአንጻሩ በቅድመ ሽያጭ ቤት የገዙ (በተለይም ዲያስፖራዎች) ቀጣይ ክፍያዎችን በወቅቱ አለመክፈላቸው በፕሮጀክቶች መጓተት ላይ የራሱን ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑ ተገልጿል።

እንዲሁም ማህበሩ ከዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ጋር በመተባበር የደህንነት ሥልጠናዎችን
እንደሚያመቻችና ደረጃውን ያልጠበቀ ማንኛውም ግንባታ እንዲታገድ ከመንግሥት ጋር የጀመረውን የጋራ ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።”





Leave a Comment