banner

ባቡል ኸይር በ1.2 ቢሊየን ብር የጀመረውን የምገባ ማዕከል ግንባታውን ለሚዲያ አካላት አስጎበኘ

👉 የተመሠረተበትን 5ኛ አመቱንም በታላቅ ድምቀት ሊያከብር ነው

ዘር ፣ሀይማኖት፣ ቀለም እና ጾታ ሳይለይ ሰው ስለሆኑ ብቻ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት የሚታወቀው ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ሰዎችን መርዳት የጀመረበትንና ታላላቅ ስራዎችን የሰራበትን ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በታላቅ ድምቀት ሊያከብር መሆኑን አስታወቀ።

ድርጅቱ የፊታችን ጥር 4 ቀን 20፞17 ከጠዋቱ 3:00 ጀምሮ «አምስት ዓመታትን በሰብአዊነት» በሚል መሪ ቃል ባቡል ኸየር አምስተኛ አመቱን አስቦ ለማዋል ቅድመ ዝግጅት ማደረጉን የድርጅቱ የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት ማህበራዊ ሀላፊነቱን በመወጣት ዜጎች ጤናማ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ ለማስቻል በቀን ሁለት ጊዜ የተዘጋጀ ምሳ እና እራት እንደ ቤተሰባቸው ብዛት እየመገበ አሁን ላይ ከ5 ሺ በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦችን የምግብ ዋስትና እና የጤና መድህናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን እና
ድርጅቱ ከ150 በላይ ለሚሆኑ ሴቶችና እናቶች ቋሚ የስራ እድሎች መፍጠሩን መስራቿ ወይዘሮ ሀናን መሀመድ በዛሬው ዕለት በግንባታ ጉብኝት እና የመግለጫ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሀናን አያይዘውም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችና ሴቶችን በተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች እንደ ልብስ ስፌት፣ የኮምፒዩተር ስልጠና ፣ የጫማ ስራ ስልጠና በመስጠትና በማስመረቅ የስራ እድሎችን ጭምር በማመቻቸት ከራሳቸው አልፈው ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ ማድረግ መቻሉን ጨምረው ተናግረዋል።

የድርጅቱ የምንግዜም አጋርና ደጋፊ እንዲሁም የበዓሉ አስተባባሪ ኮሚቴ የሆነው ወጣቱ ባለጸጋ ምረትአብ ሙሉጌታ በጉብኝት መርሀ ግብሩና በመግለጫው ላይ ተገኝቶ እኛ ኢትዮጵያውያኖች በመረዳዳትና በመደጋገፍ እንታወቃለን ይህን ቀን የምንወጣው ያለን ለሌላቸው ስናካፍልና ስንረዳዳ ነውና እንደባቡልኸይር አይነት ድሬጅቶችን ሀይማንት፣ ዘር ፣ቀለም ሳንል ከጎናቸው ሆነን የሚሠሩትን ስራ ማበረታታት እና ማገዝ ግድ ይለናል።

በተጨማሪም ባቡልኸይር ራሱን በራሱ ለመርዳት መንግስት በሰጠው መሬት ላይ ትልቅ ህንጻ ለመገንባት የጀመረው አካሄድ ይበል የሚያሠኝና የእኛን ድጋፍ የሚሻ በመሆኑ ደጋግ ኢትዮጵያውያን በቻላችሁት አቅም በማገዝ አሻራችሁን ልታሥቀምጡ ይገባል።

በተጨማሪም ለ5ኛ አመት ክብረ በአሉም ሁላችንም ተገኝተን የቻልነውን እናግዝ ሲል ጥሪ አስተላልፏል።

ባቡል ኸይር በአበበ ቢቂላ የመመገቢያ ማዕከልና የሙያ ስልጠና ማሳያ ስፍራ ጨምሮ ፣ በአቃቂ ቃሊቲ የስልጠና ማዕከል እና የህፃናት ማቋያ፣ በኦሎንኮሚ ለወጣቶች የስራ እድልን እየፈጠረ የሚገኝ የብሎኬት ማምረቻ፣ በቤተል አለም ባንክ የባቡል ኸይር የምገባና የአረጋዊያን መጠለያ ሁለገብ ማዕከል ፕሮጀክት ዋና መስሪያ ቤት ለመገንባት የከርሰ ምድር የንጹህ መጠጥ ውሃ በራስ ሙሉ ወጪ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አስመርቋል።

የመብራት ዝርጋታም በተመሳሳይ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ለፕሮጀክቱ ግንባታ አቅም እንዲሆን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ላለፉት አምስት አመታት የተራቡትን በማጉረስ፤ የታረዙትን በማልበስ፤ እንዲሁም ለበርካታ ወገኖቻችን የስራ እድል በመፍጠር በበርካታ የሰብአዊነት ተግባር ተሰማርቶ የበኩሉን በጎ ሚና ሲወጣ ቆይቷል።

ባቡል ኸየር በጎ አድራጎት ድርጅት ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጥቅምት 11 ቀን 2012 በመዝገብ ቁጥር 4513 ተመዝግቦ በሴቶች ብቻ የተመሰረተ ድርጅት ነው።





Leave a Comment