#FastMereja I በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ድርጊቱን በጽኑ በመኮነን ጥፋተኞች ላይ እርምጃ እንደሚወስድና ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሰጥ ቃል ገባ።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከመቐለ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ልዑክ ጋር ባደረጉት አስቸኳይ ውይይት ላይ እንደገለጹት፣ ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም በአክሱም ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመው ድብደባ፣ የንብረት ውድመትና የቅዱስ ቁርአን መቀደድ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው። ፕሬዝደንቱ አስተዳደራቸው ለተፈጠረው ችግር አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ሰላምን ለማረጋገጥ ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ለዝርዝር መረጃው፦
ባለፈው ሳምንት በአክሱም ከተማ ሙስሊሞች ተከራይተው በሚሰግዱበት ስፍራ ላይ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በሰጋጆች ላይ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት መድረሱን የጠቅላይ ምክር ቤቱ ልዑክ በዝርዝር አቅርቧል። በወቅቱ የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የሀይማኖት ስድብ አስመልክቶ ማብራሪያ የጠየቀው ልዑኩ፣ ለጉዳዩ አድልዎ የሌለበትና ዘላቂ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጠው አጽንኦት ሰጥቷል።
ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በሰጡት ምላሽ፣ ድርጊቱ የክልሉን የቆየ የጋራ አብሮነት የሚንድ መሆኑን ጠቅሰው፣ በደሉ በአስቸኳይ እንዲቆም ትእዛዝ መተላለፉን ገልጸዋል። የጠቅላይ ምክር ቤቱ አጣሪ ልዑክ በቀጣይ ቀናት የመፍትሔ ሃሳቦችን የያዘ ሪፖርት ለክልሉ መንግሥት የሚያቀርብ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥትም በሪፖርቱ መሠረት ተጠያቂነትን እንደሚያሰፍን ይጠበቃል። በውይይቱ ላይ የሁለቱም ምክር ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ውይይቱ በጋራ መግባባት መጠናቀቁ ታውቋል።
ሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሕዝብ ግንኙነት
