#FastMereja I ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበርክት ቆይቷል፤ አሁንም በማበርከት ላይ ይገኛል፣ ተቋሙ በስራ ዕድል ፈጠራ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ግዙፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ድርጅት መሆኑ ተገልጿል። ባለፉት ዓመታት በቢዝነሱ ዓለም በሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ከመዝለቅ በዘለለ፣ ከሚያገኘው ትርፍ 10 በመቶውን ለበጎ አድራጎት በማዋል ላይ እንደሚገኝ ተቋሙ አስታውቋል።
እንደአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በማሳደግ እንዲሁም በተኪ ምርት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው ሚድሮክ፤ ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆን ግንባር ቀደምነቱን በተግባር አሳይቷል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር መክፈሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙ ራሱ አምርቶ ለውጭ ገበያ ባቀረበው ምርት ከ390 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ማግኘቱን አስታውቋል። በተጨማሪም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ወደ ሥራ ከማስገባት ባለፈ ለኮፕ-32 (COP32) ጉባኤ የሚሆኑ አዳዲስ ሆቴሎችን እየገነባ ይገኛል።
አሁን ላይ ከ45 በላይ ኩባንያዎችን በውስጡ የያዘው ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በሆስፒታሊቲ፣ በአገልግሎት፣ እንዲሁም በኮንስትራክሽንና ሪል ስቴት ዘርፎች የተሰማራ ሲሆን፤ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ በማደራጀት አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ይህንን ዘርፈ ብዙ ስኬት ይበልጥ ለማጉላት፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እና ቀጣይ የትኩረት መስኮቹን ለማስተዋወቅ ከፊታችን ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ በአይነቱ ልዩ የሆነ “ሚድሮክ ሳምንት ኤግዚቢሽንና ባዛር” በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ተገልጿል። በዚሁ መድረክ ላይ ሁሉም የሚድሮክ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎቶቻቸውን አቅርበው የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ፣ ማኅበረሰቡም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቹን መግዛት እንደሚችል ተመላክቷል። ከዚህም ባሻገር ተቋሙ ከሚታወቅባቸው የማኅበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተነግሯል።



