#Fastmereja:-ዘምዘም ባንክ አ.ማ በ2025/26 በጀት ዓመት ከዕቅድ አንጻር አጠቃላይ የስራ አፈጻጸሙ የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከግብር በፊት ከ1 ነጥብ 56 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።
ባንኩ ይህንን የገለጸው በዛሬዉ እለት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ባካሄደው የባለአክሲዮኖች 6ኛ መደበኛ እና 5ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው።
በጉባኤው ላይ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ናስር ዲኖ እንደገለፁት ፤ በበጀት ዓመቱ የባንኩ አጠቃላይ ገቢ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ገልፀዉ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን የ144 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 20.4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ጉባኤው በተካሄደበት ዕለትም ከ22.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሻገሩ ተመላክቷል።
የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በ112 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት አሳይቶ ከነበረበት 2 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ወደ 5 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፤ አጠቃላይ የሀብት መጠኑም 76 በመቶ አድጎ 29 ነጥብ 24 ቢሊዮን ብር መድረሱም ነዉ የተገለፀዉ።
በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬት ባለሥልጣን የዘምዘም ባንክን የምዝገባ መግለጫ (Registration Statement) ማጽደቁን ተከትሎ፤ ባንኩ አክሲዮኖቹን ለህዝብ ክፍት ከማድረግ ሂደቱን ያጠናቀቀ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ ወለድ አልባ ባንክ ለመሆን መቻሉም ነዉ የተገለፀዉ።
በዲጂታል ባንክ አገልግሎቶች ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ማድረጉን ያስታወቀው ባንኩ፤ የዲጂታል ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከ106 በመቶ በላይ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ “አንሳርዲጂታል ፋይናንሲንግ” በተባለ መድረክ ለአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ ተሰማሪዎች ያለምንም ማስያዣ ከ10,000 ለሚበልጡ ደንበኞች 1 ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር የዲጂታል ፋይናንሲንግ አቅርቦት አከፋፍሏል።
የደንበኞችን ቁጥር በ56 በመቶ በማሳደግ ከ973 ሺህ በላይ ማድረስ የቻለው ዘምዘም ባንክ፤ በ130 ቅርንጫፎቹ እና ከ2,115 በላይ ቋሚና ኮንትራት ሠራተኞች አማካኝነት አገልግሎቱን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ባንኩ በበጀት ዓመቱ የGIFA ሻምፒዮንሺፕ፣ የIIFCA ምርጥ ኢስላሚክ ባንክእና የEFICA ዓለም አቀፍ ፈጠራ ሽልማቶችን መቀዳጀቱም ነዉ የተገለፀዉ።




