#FastMereja I ከታዋቂው ሩሲያዊ ደራሲ አንቷን ቼኮቭ ዘመን ተሻጋሪ የተውኔት ድርሰቶች ውስጥ ወርቃማ ተውኔቶች የተባሉትን አራት ተውኔቶች ስብስብ “የወንዜ ሳቢሳ” በሚል ርእስ በአቶ ሳምሶን ብሬ ወደ አማርኛ ተተርጉመው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ጥራዝ ታትመው በዛሬው ዕለት በወመዘክር አዳራሽ በድምቀት ተመርቋል።
“የወንዜ ሳቢሳ” በሚል ርእስ የታተመው የተውኔት ድርሰት ስብስብ አራት የአንቷን ቼኮቭ ዘመን ተሻጋሪ የምንግዜም ወርቃማ ስራዎች የተካተቱበት ሲሆን የመጽሀፉ ርእስ እንዲሆን የተመረጠው “የወንዜ ሳቢሳ” (The Sea Gull) እና “ባለ ቼሪው መናፈሻ” (The cherry Orchard) የሙሉ ሰአት ተውኔቶች ሲሆኑ “የጋብቻው ትጭጭት” (Marriage Proposal) እና “የትንባሆ ጉዳት” (On the Tarmfulness of Tobacco) ደግሞ ባለአንድ ገቢር አጭር ተውኔቶች ናቸው።
ይህ የትርጉም ስራ ለትያትርና የተውኔት ድርሰት ወዳጆች እና ለአንቷን ቼኮቭ አፍቃሪያን በስጦታነት የቀረበ እንዲሁም ለትያትር ጥበብ ማስተማሪያነት ሊያገለግል የሚችል ማለፊያ የተውኔት የትርጉም ስራ ነው ተብሏል። ተርጓሚው የትርጉም ስራውን ለመስራት ለበርካታ አመታት ከሩሲያ ቋንቋ ወደ እንግሊዘኛ የተተረጎሙ ሦስት የተውኔት ትርጉሞችን በማመሳከር ተውኔቱ ወደተጻፈበት የሩሲያ ትርጉም በእጅጉ በቀረበ ሁኔታ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ሞክሯል።
ተርጓሚው አቶ ሳምሶን ብሬ ለገሀር የጥበብ መንገዱን የጀመረው በቅዱስ ዮሀንስ ደብረነጎድጓድ ቤተክርስቲያን ፍቅረ እግዚእ ሰንበት ትምህርት ቤት የተውኔት ድርሰቶችን በመጻፍ፣በማዘጋጀትና በመተወን ለበርካታ አመታት አገልግሏል። ቀጥሎም HPDO በተባለ የህብረተሰቡን ንቃት ለማሳደግ በሚሰራ ድርጅት ውስጥ በሥነ ፅሁፍ ዘርፍና በተዋናይነት ተቀጥሮ ከአንድ አመት በላይ አገልግሏል። ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት በመግባት በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ወደ ጥበቡ አለም በመመለስም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በትያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል በማታ መርሀግብር የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በአሁኑ ወቅት ጠበቃና የሕግ አማካሪ በመሆን በመስራት ላይ ይገኛል።
በእለቱም ከመጽሀፉ ላይ የትንባሆ ጉዳት (On the Tarmfulness of Tobacco) ባለ አንድ ገቢር ባለ አንድ ሰው አጭር ተውኔት በተርጓሚው በአቶ ሳምሶን ብሬ የተተወነ ሲሆን ለአንጋፋው የጥበብ ሰው ተስፋዬ አበበ (father) የእውቅና በሰርተፊኬት ተሰጥቷል።





1 comment
ስለ ኑሮ ነው