#FastMereja I የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዝዳንት በኾኑት በጻድቁ አብዶ (ፓስተር) የተዘጋጀውና ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ያስተማሩት ትምህርት በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለኅትመት በቅቷል። በትንቢተ አብድዩ መጽሐፍ ላይ መነሻውን ያደረገውና የኹለት ታላላቅ ወንድማማች ሕዝቦችን የጥላቻና የበቀል ታሪክ የሚዳስስ ሲኾን መልእክቱ ለቤተሰብ፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ብሎም ለሀገር ያለው ፋይዳ ጉልሕ ነው ተብሏል።
መጽሐፉ 150 ገጾች ያሉት ሲኾን ሦስት ዐበይት ምዕራፋት አሉት። መነሻውን በትንቢተ አብድዩ መጽሐፍ ላይ በማድረግ የኤዶማውያንን ታሪክ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ የሚዳስሰው የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። ኹለተኛው ምዕራፍ ትኩረቱ በበቀል ምንነትና መገለጫዎች ላይ ሲኾን የኤዶማውያንን ጣምራ ኀጢአቶች በመዳሰስ የተበቃይ ፍጻሜው ምን እንደሚኾን ያሳያል። በሦስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ይቅርታና ምሕረት ብቸኛዎቹ መፍትሒዎች መኾናቸውን በማስገንዘብ ይቅርታና ምሕረት ምንድን ናቸው? ይቅርታና ምሕረት የማድረግ በረከቶችስ ምንድን ናቸው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የመጽሐፉ አኹናዊ ፋይዳ ያመላክታል ተብሏል።
በመጽሐፉ የቀረበው መልዕክት አኹን ላይ እንደ ማኅበረሰብ፣ እንደ ቤተ ክርስቲያንና እንደ ሀገር ላለንበት ኹኔታ የራሱን መፍትሄ የሚያመላክትና የዕርቅን ጥሪ የሚያስተጋባ መጽሐፍ እንደሆነ ተገልጿል።
የምረቃ መርሓ ግብሩ እሑድ ሰኔ 08/ 2017 ዓ.ም. የቤተ እምነት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ እንግዶች በተገኙበት በዐድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ከ9፡00 ሰዓት ጀምሮ በልዩ ኹኔታ ይመረቃል።
ፓስተር ጻድቁ አብዶ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መድረኮች ያስተማሩት ይህ ትምህርት አኹን ላይ በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ለመቅረብ ብዙ ጊዜያትን የፈጀ ሲኾን ትምህርቱን ለአንባቢያን በሚኾን መልኩ በመጽሐፍ ለማዘጋጀት ብዙዎች በገንዘብ በጉልበት እና በዕውቀት እንደተሳተፉበት ተነግሯል።





3 comments
እንዴት ያለ አንብቡኝ የሚል ርዕስ ነው አቦ!
የእግዚአብሔር ቃል የሚለው ግን ይቅርታና ምህረት የዘለዓለም ናት ነው ሚለው
በቀል በቀለኛውን ያጠፋዋል” ፓስተር ፃዲቁ በሰላም ነው ?