«ለሕይወት ቅድሚያ እንስጥ!» በቢሾፍቱ ከተማ ሃገራዊ የመንገድ ደህንነት ንቅናቄና የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ መርሐ-ግብር ሊካሄድ ነው
#FastMereja I የመንገድ ትራፊክ አደጋ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ የጤናና የኢኮኖሚ ስጋት እየሆነ የመጣበትን ሁኔታ ለመቀነስ እና የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ሃገራዊ ንቅናቄ በቢሾፍቱ ከተማ ሊካሄድ መሆኑን ኪዲ ፋውንዴሽን አስታወቀ።
በትራፊክ አደጋ ሕይወቷን ባጣችው ቅድስት ክፍሌ ወልደማርያም መታሰቢያነት በካናዳ የተመሠረተውና በመንገድ ደህንነት ላይ የሚሠራው ይህ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት፤ የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ማኅበረሰብ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጻል።
ፋውንዴሽኑ የመንገድ ደህንነት ግንዛቤን ማሳደግ፣ ለአደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት እና ከአደጋ በኋላ ለተጎጂዎች አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ማኅበራዊ ድጋፎችን ማመቻቸት ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ አስታውቋል። ድርጅቱ «ለሕይወት ቅድሚያ እንስጥ!» በሚል መሪ ቃል በሚያካሂደው በዚህ እንቅስቃሴ አደጋዎችን ከመከላከል ባሻገር፤ አደጋ ሲደርስ ፈጣን ምላሽ መስጠት እና የሰው ሕይወት ክብርን የሚያስቀድም ማኅበረሰብ መገንባት ዋና ዓላማው እንደሆነ ከወጣው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
የዚሁ ንቅናቄ አካል የሆነ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫና የእግር ጉዞ መርሐ-ግብር ኅዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም በቢሾፍቱ ከተማ ይካሄዳል። በዝግጅቱም ከ5,000 በላይ ተሳታፊዎችን በአንድ የመነሻ መስመር ላይ በማሰለፍ የመንገድ ደህንነት መልዕክትን ለማስተላለፍ የታቀደ ሲሆን፤ ከመንግሥት ተቋማት፣ ከግሉ ዘርፍ፣ ከጤናና ትምህርት ተቋማት፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከሲቪል ማኅበራት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ነው።
በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የመንገድ ደህንነት መልዕክቶችን ለመላው ማኅበረሰብ በማድረስ፣ አሽከርካሪዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ እና ወጣቶችን የለውጥ አካል በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፤ በኅዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም በቢሾፍቱ በሚካሄደው በዚህ ታላቅ መርሐ-ግብር ላይ በመገኘት የንቅናቄው አካል እንዲሆኑና ዘገባዎችን ለህዝብ እንዲያደርሱ ጥሪ አስተላልፏል።




